Wednesday, 5 March 2014

ትዝብት፡አንድ በእድሜ ጠና ካሉ ሽማግሌ ጫማ አሳማሪ ጫማየን እያሳመሩልኝ ሳለሁ እኒሁ ሰውየ ከጎናቸው ካለ ሌላ ጫማ አሳማሪ ጋር ታውቃለህ አላውቅም በሚል እሰጣ ገባ ውስጥ ይገባሉ፡፡እኔም የሁለቱንም ክርክር/ጭቅጭቅ/ ጥሎብኝ ዝም ብየ እየሰማሁ ዕያለ የእኔው ሰውየ ልክ ጉዳዩን እንደማውቀው አድርገው አይደል እያሉ በመሀል በመሀሉ ጠቆም ጠቆም ያደርጉኛል፡፡
ከዛም ለጭቅጭቃቸው ማስረጃ እንደሚሆናቸው በማሰብ እኔንም የጭቅጭቃቸው አካል ለማድረግ እየሞከሩ አሁን ይህ ሰው/ተከራካሪቸው መሆኑ ነው/ ትልቅ ሰው ነው፤ይሄ ጉዳይ የሚያቅተው ይመስልሀል፤ ከሉኝ በኋላ ቀጥለው እኔ እንኳን ይሄን ቤት በደንብ አድርጌ መስራት እችላለሁ፤ለመሀንዲስ ምንም አላወጣም፡፡ማገሩን፣ቆርቆሮውን ፣ሚስማሩን በደንብ በደንብ አድርጌ ነው የምሰትረው ፣ያው መሀንዲስ ነኝ እያሉ ሲጨቀጭቁኝ እንደማንግባባ ብገምትም ዝም ማለቴን ከክፋት እንዳይቆጥሩብኝ በመስጋት ልክ ነዎት እርሰዎ ቤት ሊሰሩ ይችላሉ ምህንድስና ግን አሁን እርሰዎ የጠቀሷቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ብየ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለማብራራት ስሞክር ታዲያ ምኑ ቀረ ምህንዲስና ማለት እኮ ይኸው ነው፤ሰው ሰነፍ ሰለሆነና ገንዘብ መክፈል ስለሚፈልግ ነው እንጂ በዛ ከተባለም ተመሳሳይ ቤት ፎቶ አነሳና አስመስየ ነው ቁጭ የማደርገው እያሉ ሲቀጥሉ ቀድሞ ወደነበረው ዝምታየ ተመለስኩኝ፡፡ከዛም በአሸናፊነት መንፈስ አትችለኝም እኮ፤አሸነፍኩህ አይደል እያሉ መኮፈሳቸውን ቀጥለው የእኔንም ጫማ አሳምረው ጨርሰውልኝ ሂሳባቸውን ከፍየ ከእሳቸው ተለየሁና ተገላገልኩ፡፡
እኔ የምለው የዚህ ሽማግሌ ለምህንድስና  ያላቸው ግምት ሲገርመኝ ለመናገር እንጂ ለማዳመጥ አለመፈለጋቸው ግን ደነቀኝ፡፡ጉዳዩም ብዙ ጊዜ ተደጋገመብኝ፡፡ካላዳመጥንስ እንዴት እንግባባለን፡፡

እረ እንደማመጥ!!!